Sunday, December 9, 2012


By  Fekadu Andargie


TV room ዛሬ

ማታ የዜና ሰዓት ጠብቄ ወደ ቲቪ ሩም ጎራ ማለት ዘና ያደርገኛል ፡፡ በየቀኑ ፈገግ የሚያሰኙ ብዙ ብዙ ሽሙጦችን በነፃ ቲቪ ሩም እኮመኩማለሁ፡፡ እዚህ ቲቪ ሩም ከአፍላ ወጣት የነብር እጣት እስከ ታላላቅ በእድሜ እና በስራ ልምድ የዳበሩ የህግ ባለሙያዎች ይታደሙባታል……ዛሬ ደግሞ ምን ያወሩ ይሆን በሚል

በትናትናዉ ዕለት ምሽት ዜና አንባቢዉ “ዜና እረፍት” ብሎ ሲጀምር የሁሉም ጆሮ ቀጥ አለ፡፡ ዜና አንባቢዉ ቀጠለና “ዶ/ር እንቶኔ የዚህ ተቋም እንትን የነበሩ የታፈሩ፣ የተከበሩ አረፉ፡፡” ብሎ ዜናዉን ሲጨርስ አንዱ “እንዴት ደነገጥኩ ደብቀዉ ደብቀዉ እንዲህ በቀላል ዛሬ አረዱን ብዬ” ሲል ሌላዉ ደ
ግሞ “ቅድሚያ ስንት የሞተ እያለ እንዴት ዛሬ ሙቶ ዜና እረፍቱ ይነገራል” ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ “እኔ ገና ዶ/ር እንትና ብሎ ሲጀምር ነዉ አለመሆኑን ያወቁት” ፣ ታማኞች ደግሞ “ዜና እረፍት ሲባል የጨዉ አምድ መስለዉ ቆይተዉ ሌላ መሆኑን ሲያዉቁ ተንፈስ” እያሉ ቲቪ ሩም የሽሙጥና የሃሜተኛ ቤት መስሎ አምሽቶ ነበር፡፡

ዛሬ ደግሞ ሌላ ሰማን ዜና አንባቢዋ ትምህርት ጥራትን በተመለከተ ስለተደረገ ስብሰባ ትንሽ ያቅሟን ካወራች በኋላ የትምህርት ሚኒስቴሩ ቀርበዉ ለተሰብሳቢዉ እንግሊዘኛ ሲያነቡ ቲቪ ሩም የነበሩ በሚኒስቴሩ እድሜ እኩያ የሚሆኑ እንዲህ ሲል ተደመጡ “እንዴ! እንግሊዘኛ ማንበብ ይችላል እንዴ?” ሲሉ

ሌሎቹ በመገረም እንዴት ማንበብ አይችልም ? ብለዉ ጥያቄን በጥያቄ ሲያፋጥጧቸዉ
“አይ ፊርማ ብቻ የሚችል ስለሚመስለኝ ነዉ፡፡” ብለዉ እርፍ……

”ፊርማ ብቻ የሚችል” ያሉበት ምክንያት ይህ ሚኒስቴር የአሁኑን ማዕረግ ከማግኘቱ በፊት ክልል ሶስት የነበረ ሲሆን በኢትዮ- ሱዳን ድንበር ጎንደር አካባቢ የነበረዉን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ለሱዳን ሲሰጥ አብዛኛዎቹ የክልሉ ባለስልጣናት አንፈርምም ሲሉ እሱ የአሁኑ ትምህርት ሚኒስቴር ፈርሞ ነዉ ወደ ሚኒስቴር ደረጃ ያደገ እየተባለ ስለሚታማ ነዉ፡፡

የስፖርት ዜና ላይ ደግሞ ዛሬ በ5000 ማጣሪያ ከመጀመሪያዉ ምድብ አንደኛ የወጣዉ ለአዘርባጃን የሚሮጠዉ በትዉልድ ኢትዮጵያዊ የሆነዉ ዜግነቱን የቀየረዉ እንቶኔ ነዉ ሲል…. ከቲቪ ሩም አሽሟጣጮች ምነዉ ሯጮቻችን እንዲህ ዜግነትን መቀየር “ፖለቲከኞቻችንም ዜግነት እየቀሩ ሌላ ሃገር በመሩ፣በሌላ ላይ በሰለጠኑ ”ሲል

ሌላኛዉ ቀበል አድርጎ “እሱማ የት ይቀራል ለጊዜዉ እነሱ ዜግነት ቀይረዉ እየመሩን ቢሆንም አሁንም እርቀዉ ሳይርቁ ወደ ጎረቤት ሃገር ዜግነታቸዉን መቀየራቸዉ የት ይቀራል” ሲል

እኛም ከጎረቤት የተባለዉ ከኤርትራዊ ወደ ኢትዮጵያዊ እንደገና ከኢትዮጵያዊ ወደ ኤርትራዊ ይሆን አልን .... እንደገና “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን ይቀይራልን” የሚለዉ ቅዱስ ቃል ትዝ አለን መለስ ብለን ግን ዜግነት እና መልክ የተለያዩ መሆናቸዉን ስናስታዉስ ሆዳችን ባባ

ያለን አማራጭ የነገን ቲቪ ሩም መናፈቅ

No comments:

Post a Comment